Insightful articles and discussions to broaden your outlook.

My Perspective. Logo: A stylized representation of the company's name, with vibrant colors and modern design. Explore diverse perspectives on tech, culture, and lifestyle at My Perspective. Discover insightful articles and discussions to broaden your outlook.

የፈራረሰ ህልም፣ የኤርትራ እውነታ

ቅዳሕ ትግርኛ

የፈራረሰ ህልም፣ የኤርትራ እውነታ

በአንድ ወቅት በአርባምንጭ እየኖርን ሳለ፣ የኤርትራ ጊዜያዊ መንግሥት ልኡካን ቡድን የነጻነት ምርጫውን ለመከታተል ወደ ዛው ደርሶ ነበር። የምርጫው ሁኔታ አወዛጋቢ ነበር ። ምክንያቱም በወቅቱ የተሰጠው ምርጫ በባርነት እና በነፃነት መካከል ያለው ምርጫ ነበር። ባርነትን ማንም ሰው ስለማይመርጥ ፣ የማይመስል ኣማራጭ ነበር ቢባል እዉነትነት አለዉ። ምርጫው ነፃነት እና ከኢትዮጵያ ጋር በመቆየት መካከል ቢሆኑ ኖሮ ምናልባት አንዳንድ ከኢትዮጵያ ጋር መቆየትን ሊመርጡ ይችሉ ነበር። ሆኖም የሰጡት ብቸኛው አማራጭ ነፃነት ስለነበር ፣ 99% ኤርትራውያን ነፃነትን መርጠው ነበር። ለ30 ዓመታት የተጋደሉበት ምክንያትም ይኸው ነበር፣ ከጭቆና ነጻ መውጣት ነበር ዓላማው። ከሱዳን፣ ከየመን፣ ከጅቡቲ ወይም ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ግንኙነት ምንም ይሁን ምን፣ ከሁሉም በላይ ወሳኙ ነገር ነፃነትን ማስከበር ነበር ዋናው።

ያኔ ኤርትራዊያን በደርግ ዘመን ብዙ ችግር በማሳለፋቸው ፣ መንግስታቸውን ለመደገፍ ደስተኛና ጉጉ ነበሩ። የነፃነት ፍላጎት ስለነበረ ፣ ሁሉም ነገር እንዲሳካ ከኣቅም በላይ በመግፋት ነገሩን ለማሳካት ተሞክሮዋል። ኤርትራ አዲስ፣ ነፃ፣ ያልተበላሸች እና የጠራች አገር ትመስል ነበር። በሌላ በኩል ደሞ የጊዜያዊው መንግሥቱ ፕሮፓጋንዳ ከፍተኛ ስለነበር ፣ በኢትዮጵያ ዉስጥ ለሚኖሩ ኤርትራዊያን የኤርትራ መታወቂያ ካርድ ከሌላቸው ፣ ከኢትዮጵያውያን ለሚመጣ ማንኛዉንም ጉዳት የመከላከል ምንም እይነት ድጋፍ እንደማያደርጉ ያስጠነቅቁ እና ፣ የማስፈራሪያ ፕሮፓጋንዳ ይለቁ ስለነበረ ፣ ሰዉ ቢወድም ባይወድም የመታወቂያ ካርድ ለማግኘት ይሽቀዳደም ነበረ።

በምርጫው ዝግጅት ወቅት የኤርትራ ጊዜያዊ መንግስት ጊዜያዊ መታወቂያ ካርድ ለኤርትራዊያን ያድል ስለነበረ። እኔም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ስለነበርኩ ምንም እንኳን ከቤተሰቦቼ ርቄ ብኖርም ፣ የኤርትራዊ መታወቂያ ለማግኘት ወደ መመዝገቢያው ቦታ ሄጀ ነበር። ትውልደ ኤርትራዊ ብሆንም ማንነቴን ለማረጋገጥ ሶስት ምስክሮች ያስፈልጉኝ ነበር። እዛ የነበሩት ሰዎች የወላጆቼን ከኤርትራ የመነጩ ስለመሆናቸው መርምረው መታወቂያው እንደሚገባኝ ወሰኑ። እንዲያዉም ከመካከላቸው እንዱ ሰው ፣ ይህ ሰው የምር ኤርትራዊ ባይሆን ኖሮ፣ ኤርትራዊ ነኝ ኣይልም ሲልም ሰምቸዋለሁ። በወቅቱ ከአንድ ኤርትራዊ ተማሪ ጓደኛዬ ጋር አብረን ስለነበር። ባለሥልጣናቱ ጉዳያችንን ተረድተው ፎቶግራፎቻችንን በማንሳት እያንዳንዳችንን 5 የኢትዮጵያ ብር እንድንከፍል ጠየቁን። ተማሪ ስለነበርን ግን ገንዘቡ አልነበረንም። ሰዎቹ ገንዘብ የለንም ማለታችንን ስላልተቀበሉን ግን ሊመዘግቡን አልፈቀዱም። ልክ ኤርትራዊነታችንን የከለከሉን ይመስል እያጉረመረምን ትተናቸው ወደ ከተማ ገሰገስን። በኋላም በዚህ ምክንያት መታወቂያ ከሚከለክሉን፣ ለሁለታችንም የሚያስፈልገውን 10 ብር ለማግኘት በሚል እሳቤ የምወዳትን ጃኬቴን ለመሸጥ ወሰንኩ። ጃኬቴን በሲቀላ ገበያ ሸጠን ክፍያውን ለማድረግ ወደ ቦታው ተመለስን። በመጨረሻም፣ የኤርትራዊ ማንነት መታወቂያችንን እንደምናገኝ በመተማመን ወደ ማደሪያችን (ግቢ) ተመለስን።

የአዲስ አበባው ክስተት

የነጻነት ምርጫ ከመደረጉ በፊት በአዲስ አበባ ኤምባሲ ውስጥ ከአንድ ኤርትራዊ ካድሬ ጋር በተደረገ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ነበር። በውይይቱ ወቅት አንዲት ሴት በሪፈረንደም ድምጽ መስጫው ወቅት ኢትዮጵያውያን ሊያደርሱት ስለሚችሉት ጥቃቶች ስጋት እንዳደረባት ተናግረች። ካድሬው ግን እንዲህ ሲል መለሰላት፣ አሁን በአስመራ ኤርፖርት የሚገኘው የኤርትራ ኮማንዶ ቡድን ዝግጁ መሆኑን እና አዲስ አበባን በአንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር እንደሚችሉ ገለጸላት። እኔም የኤርትራ ኮማንዶዎች እንደዚህ አይነት ተአምራዊ ስራዎችን ሊሰሩ እንደሚችሉ በማሰብ እየተገረምኩ ስብሰባዉን ትቼ ወደ ቤተ ገሰገስኩ። በዛን ጊዜ በአዲስ አበባ የሚገኙ ኤርትራውያን ፣ በሻቢያ ላይ ያላቸው እምነት ትልቅ ነበር። ይህም የሆነው ከእውነታው የራቀ እና እጅግ የበዛ ፕሮፓጋንዳዎች በጊዜያዊው መንግስቱ ይተላለፍ ስለነበረ ነው። የአገዛዙ ስልት ዜጎቻቸዉን እና ወታደሮቻቸዉን መረጃ እንዳይኖራቸው በማድረግ፣ ያሻቸዉን የማድረግ ስልት ነበር የሚጠቀሙት።

ጉዞ ወደ ኤርትራ ፣

በ1996 መገባደጃ ላይ ወደ ኤርትራ ለመጓዝ በወሰንኩበት ወቅት በመቀሌ ኢትዮጵያ በመሃንዲስነት ስራ ተቀጥሬ እሰራ ነበር። በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል በነበረው ግንኙነት መሻከሩን ተከትሎ በመቀሌ ያለው ሁኔታ ውጥረት ነግሶ ነበር። አንዳንድ ኤርትራውያን በመቀሌ ሞተው የሚገኙም ነበሩ፣ ለሞታቸው ሃላፊነት የሚወስድ አካልም አልነበረም። ለደህንነቴ በመፍራቴ ከተማዋን ትቼ ወደ መሃል ሃገር ከመሄድ ወደ ኤርትራ መሄድን መረጥኩ። አስመራ ስገባ በመጀመሪያው ጊዜ ላይ ብቻዬን ነበርኩ፣ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ አንዳንድ የቤተሰቤ አባላት ከኢትዮጵያ ተባርረው አስመራ ገብተው ነበር።

ወደ አስመራ የተደረገው ጉዞ በሚኒባሶች ከከተማ ወደ ከተማ ያለዉን አጭር ጉዞ ማድረግን ያካትታል። ከመቀሌ ወደ አዲግራት፣ ከዚያም ከአዲግራት ወደ ሰንአፌ፣ በመጨረሻም ከሰንአፌ ወደ አስመራ ተጓዝኩ። ከሰንአፌ ውስጥ አውቶቡስ ስጠብቅ አንድ ለየት ያለ ሰው ከቡና ቤት ወደ ቡና ቤት ሲከተለኝ አስተዋልኩኝ። በዚያን ጊዜ, እሱ የደህንነት ወኪል መሆኑን አላወቅኩም ነበር። ከብዙ ጥበቃ በኋላ አውቶቡሱ ተሳፋሪዎችን ማሳፈር ጀመረ እና የመጀመርያው ተሳፋሪ እኔ ነበርኩ። ይከተለኝ የነበረው ያው ሰው አጠገቤ ተንደርድሮ መጥቶ ከኔ ጋር ተቀመጠ። ቀኝ እጄን ሳነሳ በአጋጣሚ ደረቱን ስነካው ከጃኬቱ ስር ሽጉጥ ስለመኖሩ ተሰማኝ። የደህንነት ወኪል ስለመሆኑ ቢገባኝም ምንም ሳላደርግ ወደ አስመራ ጎን ለጎን ተቀምጠን አብረን ተጓዝን።

ደቀመሃሬ እንደደረስን ትግርኛ እደምችልና ኤርትራዊ ስለመሆኔ ጠየቀኝ። ወዴት እንደምሄድ እና ለምን እንደምሄድ ማወቅ ፈልጎ በድጋሚ ጠየቀኝ። ሁሉንም ነገር ገለጽኩለት፣ እሱም በጥሞና አዳመጠ። አማርኛ አቀላጥፎ ይናገራል ። ስለ ሙያዬና መዳረሻዬም ጠየቀኝ። አስመራ እንደደረስን አሰናበተኝና፣ ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት ወደምቆይበት ወደ አክስቴ ቤት አመራሁ ።

በማግስቱ ጠዋት ለስራ ጠርቶኝ ከነበረ ድርጅት ቢሮ ሄድኩኝ። ወደ ቢሮው ስጠጋ ፣ ያው ሰው ከህንጻው ፊት ለፊት ቆሞ አየሁት። ከሩቅ አየኝና ፊቱን በፍጥነት አዙሮ ከቢሮው በፊት ባሉ አበቦች ላይ ሲሸና በማየቴ ተገረምኩ። በአከባቢው ደሞ ሊሎች ሰዎችም ነበሩ። ቆይቶ ሰዉዬው ሰላም ሳይለኝ ወደ መዉጫው በር እየገሰገሰ ሲሄድ አየሁት ። ይህን ያልተለመደ ነገር በማየቴ በመገረም እንደ አዲስ ሰራተኛነት ምዝገባዬን አጠናቅቄ ለምሳ ወደ ከተማ ተመለስኩ።

ምሳዬን ለመብላት ወደ ምግብ ቤት ገብቼ እየበላሁ ሳለ፣ ያው ሰውዬ ወደ ምግብ ቤቱ ገብቶ ስሜን ጠራ። በመገረም እኔ እዚያ መሆኔን እንዴት እንደሚያውቅ እና እየተከተለኝ እንደሆነ ጠየቅኩት። እሱም “አይ፣ እዚህ አካባቢ ነው የምሰራው” ሲል መለሰ። ምሳዬን ጨርሼ ወጣሁ። በማግስቱ ወደዚያው ምግብ ቤት ተመለስኩኝ እና እንደገና፣ ከደረስኩ ብዙም ሳይቆይ ብቅ አለና ሰላምታ ሰጠኝ። ይህ ክስተት በመደጋገም ከሶስት ሳምንታት በላይ ቀጠለ። እሱ ሆን ብሎ እየተከተለኝ እንደሆነ ስለተረዳኝ ይበልጥ ብስጭት እና ፍርሃት አደረብኝ። እንደዚህ ያለ ሁኔታን መርዳት የሚችል ከቤተሰብ በስተቀረ ሌላ የሚረዳኝ ሰው አጠገቤ አልነበረም። አእምሮዬ ከእውነታው የራቁ ነገሮችን በማሰላሰል ሁኔታዎችን እና ነገሮችን ማያያዝ ጀመረ።

በሌላ ቀን ይህ ሰው እንደገና እንደዚሁ ቀረበኝ፣ እኔም በቁጣ ቀድሞ ያውቀኝ እንደሆነ እና ለምን እንደሚከተለኝ ጠየቅኩት። ተረጋጋ አለኝና ምሳ ከበላሁ በኋላ ቡና እጋብዝሃለሁ አለኝ፣ነገር ግን ፈቃደኛ አልነበርኩም። ከምሳ በኋላ በቅርብ ከሚገኘው ቡና ቤት ሄጄ ቡና አዘዝኩ። ቡናዬን እየጠጣሁ ሳለ ሰውየው እንደገና መጣ። በጣም ተናድጄ ለመዉጣት ስሞክር ፣ እሱ ግን ተረጋጋ ፣ አትጨነቅ አለና፣ የደህንነት ወኪል ስለመሆኑ አስረዳኝ። እስከዚያ ቀን ድረስ ከኢትዮጵያ ድንበር ጀምሮ ይከተለኝ እንደ ነበርና፣ አሁን ግን ንፁህ ሰው ስለመሆኔ አንደ አረጋጠ ነገረኝ።

አሁን ሳስበው በድብቅ የሚከተለኝ ሌላ ሰውም እንደነበር ይገባኛል። ምክንያቱም ሰውዬው ሳያየኝ የትኛውም ቡና ቤት ከገባሁ ወደ ቡና ቤቱ መጥቶ ሰላም ይለኝ ነበር። ይህ በድብቅ ሌላ ሰው የሚከታተለኝ እና መረጃ የሚያደርስ እንዳለ ይጠቁማል።

እንዲህ ሲልም ነገረኝ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የተቃዋሚ ቡድን አባል ስለመሆኔ ተጠርጥሬ እንደነበር ገለጸልኝ ። አሁን ግን ነጻ ሰው ስለመሆኔ ነገረኝና እንኳን ደስ አለህ አለኝ። ከንግዲህ ምንም አይነት ክትትል እንደማይኖር አረጋግጦልኝ እና ከዛም ሚስቱን እንደ ሚያስተዋውቅኝ ነግሮኝ ተለያየን። ከዛ ብኋላ ይህን ሰው አስመራ ከተማ ዉስጥ በአጋጣሚ እንኳን አይቼዉም አልዉቅም ነበር። በሁኔታዎች እና ባጋጠመኝ ግልጽ ክትትል ተገርሜ ነበር። ለነገሩ የሆነው ሁሉ እስከ ዛሬም ድረስ ይገርመኛል።

በኢትዮ ኤርትራ ድንበር ላይ የነበረው ሁኔታ፣

በኤርትራ ድንበር ኤርትራውያን ወደ ኤርትራ እንደገቡ በተለየ ክፍል ውስጥ ምርመራ ይደረግላቸው ነበር፣ ኤርትራዊ ያልሆኑ ሰዎች ደግሞ ለተወሰኑ ቀኖች በነጭ ወረቀት ፍቃድ ይጻፍለትና ፣ እንደ ቪዛ ማለት ነው፣ ወደ ኤርትራ እንዲገባ ይፈቀድለታል። ይህም የሚሆነው በተለያዩ ክፍሎች ዉስጥ ነው። ኤርትራዊ ከሆንክ እዚህ ክፍል ግባ ፣ ካልሆንክ ደሞ ወደዛኛው ክፍል ግባ ትባልና፣ ኤርትራውያን ስለ መድረሻቸው፣ ስለዘመዶቻቸው እና ስለጉዞአቸው ዓላማ ብዙ ይጠየቃሉ። በድብቅ፣ የደህንነት ወኪል እንዲከታተላቸው ይመደባል ፣ እኔው ላይ እንደተመደበው ማለት ነው። የሚገርመው በኤርትራ ያሉ ባለስልጣናት የሚፈሩት ኢትዮጵያውያን ሳይሆን ከኢትዮጵያ ለሚመጡ ኤርትራዊያን ነበር። ስለዚህም ነው ጥብቅ ክትትል በኤርትራዊያን ላይ የሚደርጉበት ምክንያት። ወደ ኤርትራ ስገባ የመጀመሪያ ልምዴ ይህ ነበር፣ እናም ይሄ በእኔ ላይ ዘላቂ የሆነ ስሜት ፈጥሮብኝ ነበር።

በኤርትራ ያለው ከባድ እውነታ ፣

በ 1996 ለመጀመሪያ ጊዜ ኤርትራ ስገባ የተገነዘብኩት እዉነታ በጭንቅላቴ ከነበረው ግንዛቤ ፈጽሞ የተለየ ነበር። የጠበኳቸው ጠብደል ኮማንዶዎች የትም አይታዩም። የመንግስት ወታደሮች በቂ ምግብ እንኳን የሚበሉ አይመስሉም ነበር። እንዲያዉም ብዙዎቹ ፣ መሳሪያቸውን እንኳን ለመሸከም የሚቸገሩ አይነት ሆነው ነው ያገኘኋቸው። አዲስ አበባ ውስጥ እያለሁ የሰማኋቸውን የታዋቂ ኮማንዶዎችን ታሪክ በተመለከተ ላቀረብኩት ጥያቄ፣ አንድ በሃልሃል ትንሽ መንደር ዉስጥ የሚኖር ጃንሆይ የሚባል የጦር ካምፕ መሪ አስሮ አሰቃይቶኛል። ከዛፍ ላይ ታስሬ በጭካኔ ተደብድቤያለሁ። ባለ ሙያ እንደመሆኔ መጠን ሀገሬን የማገልገል ጉጉት ስለነበረኝ ነበር ወደ ሃገሬ የገባሁት፣ ቢሆንም ግን እንደዚህ አይነት አረመኔያዊ ድርጊት እና ህገወጥ ድርጊት በመመልከቴ በወቅቱ በጣም ኣዝኜ ነበር ፣ ከዚህም የተነሳ የተስፋ ቢስነት ስሜት ይሰማኝ ጀመረ። ከጋርዮሽ ስረዓተ ዘመን በፊት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሕይወትና ጭካኔ የተሞላበት የሚመስል ኑሮ ስለታዘብኩ፣ ወደ ቀደመው ዘመን የተጓዝኩ ያህል ሆኖ ተሰማኝ። በህይወቴ ማንም እንደዛ ደብድቦኝ ወይም ገርፎኝ ስለማያዉቅ፣ ወደ ጨካኝ ህብረተሰብ የተቀላቀልኩ ስለመሆኑ ጥርጥር አላደረብኝም። ያዉም ምንም ሳላደርግ። የሆነ ነገር አድርጌ ቢሆንማ ኖሮ፣ የግፍ ግፍ ይወርድብኝ ነበር ማለት ነው።

ወደ አስመራ ተመልሼ በሃልሃል ስላለው ሁኔታ ለአለቆቼ ስነግራቸው ምላሻቸው አስገርሞኛል። ‘ ሊገድሉህ ይችሉ ነበር’ ብለው ነበር የመለሱልኝ። ምላሻቸው በጣም ነበር ያስገረመኝ።

ከሲቪል ልምዶቼ በላይ፣ በ SAWA በውትድርና ያሳለፍኩት ቆይታ የኤርትራን ጭካኔ አጋልጦልኛል። በሦስተኛው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት ወቅት እንደ ሰው ፈንጂ አጽጂ ሆኜ በፈንጂ ላይ ለመራመድ ተመርጬ ነበር። እንዲህ ነበር የሆነው፡- ከተኛንበት ቦታ 12 የሚሆኑ ሰልጣኞች ያለምን ኮሽታ ተመርጠን ወደ ለየት ያለ ቦታ ወሰዱን፣ ከዛም ሊሆን የታሰበዉን አስረድተዉን ፣ለመሞት እንድንዘጋጅ ነገሩን። የያዝነዉን እቃ ጥለን አንሶላ ብቻ እንድንይዝ ተነገረን። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ማንም ሰው ከጓደኞቼ የሚያዉቅ ሰው አልነበረም፣ ምክንያቱም በጨለማ ከተኛንበት ቀስ ብለው እየቀሰቀሱ፣ አጠገብ የተኛው ሰው እንኳን ሳይሰማ ነበር ያስነሱን ።  አላማው፣ ፈንጂዎቹን ረግጠን በመውጣት ለሌሎች ወታደሮች በሰላም እንዲያልፉ ለማድረግ ነበር። በነሱ ዓይን፣ እኛ እንደማንጠቅም ተቆጥረን እና ለመሞት የተዘጋጀን ነበርን። ከሁሉም በላይ ደሞ፣ በነዚህ ሰዎች ከንቱ ወይም ዋጋ ቢስ መባሉም በጣም ያማል። በእግዚአብሔር ቸርነት ግን  እኛን ሊያጓጉዘን የነበረው ተሸከርካሪ በጊዜው አልደረሰም ነበር። በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያ ጦር የኤርትራን ሃይሎች ወደኋላ በመግፋት  ከዚህ አስከፊ እጣ ፈንታ አዳነን።

ይሚገርመው በምናቤ ያሰብኳት ኤርትራ እና በዉን ያገኘሁዋት ኤርትራ ኣልተገጣጠሙብኝም ። ከ30 አመታት ትግል በኋላ ኤርትራ በደንብ ተደራጅታ በተሻለ ሁኔታ የምትተዳደር ትሆናለች ብዬ አምን ነበር። ነገር ግን ያገኘሁት የተዘበራረቀና ትርምስምስ ያለ አስተዳደርን ነበር። ይህ በቅጡ ያልተደራጀ ቡድን በሚገባ የተደራጀውን የኢትዮጵያ ጦር እንዴት ማሸነፍ እንደቻለ እንኳን እስከ ዛሬ ሳስበው ግርም ይለኛል ።

በአሰብ ከተማ ወታደራዊ አገልግሎት፣

በአሰብ ከተማ በዉትድርና ባገለገልኩበት ወቅት በመመገቢያ ካፍቴሪያችን ውስጥ ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ በእንዲህ መልክ ነበር ያስተዋልኩት። ከጀርመን የተበረከተ ጊዘው ያለፈበት የወተት ዱቄት እና ያልጸዳ ምግብ ይቀርብልን ነበር። አንድ የምንበላው በጣም ጤናማ ያልሆነ የምግብ አይነት “ቦጅቦጅ” የሚባል ምግብ ነበር። እያንዳንዱ ሰው ሁለት ቁራሽ ዳቦ ይሰጠዉና ዳቦዉን ቆርሶ በትልቅ የመመገቢያ ሰሃን ላይ በመቀላቀል ከሌሎች 7 ሰዎች ጋር በአንድላይ ሆኖ ይመገባል፣ አንድ ሰው ወጥ ለማግኘት ምግቡን ወደ ኩሽና ቤት ይዞ በመሄድ ወጥ ያስደርግበታል። ከዚያም በህብረት እንመገባለን ማለት ነው። የምንመገበው የወጥ ይዞታም በተለምዶ ቲማቲሞችን፣ ዘይትን፣ ውሃን፣ ሽንኩርትን፣ ቀይ በርበሬን እና ጨውን ያቀፈ ሲሆን ፣ ይህም ምንም ተጨማሪ ለሰዉነት ጥቅም የሚሰጡ ንጥረ ነገሮች የሌለው የምግብ አይነት ነበር ። ይህም የአመጋገብ ስርዓት ፣ በሃላፊዎቹ ዘንድ በወታደሮች መካከል ጓደኝነትን እና ወንድማማችነትን የሚያሳድግ ነው ብለው ያምኑበት ስለነበር፣ በቡድን እንጂ በተናጠል ምግብ መብላት እይፈቀድም ነበር።

የአሰብ ከፍተኛ ሙቀት፣ ብዙ ጊዜ ከ40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ስለነበር፣ ሙቀቱ ጉዳዩን የበለጠ ውስብስብ አድርጎት ነበር። በዛ ሙቀት ሽንት ቤት በምንጸዳዳበት ግዜ ፣ ወረቀት ከመጠቀም ዉሃን ነበር እንደ መጸዳጃ የምንጠቀመው። ለነገሩ ወረቀትም ቢሆን ስለሌለ ዉሃን መጠቀም ብቸኛው አማራጫችን ነበር። ጉዳቱ ፣ መጸዳጃ ቤቱ ከምግብ ቤት ፊት ለፊት የሚገኝ በመሆኑ ወታደሮቹ ሽንት ቤት ተጠቅመው በቀጥታ ወደ ካፍቴሪያው ነበር የሚያቀኑት። ከምግብ በፊት ወደ ሽንት ቤት ነበር የሚገባው። ብዙ ጊዜ በበቂ ሁኔታ መጸዳዳት ስላልነበረ ፣ ለሌላው ሰው ጤንነት አደገኛ ነበር። አብዛኛዎቹ የብሄራዊ አገልግሎት አባላት ደሞ መሰረታዊ የንፅህና እውቀት ወይም ትምህርት ስለሌላቸው፣ የጤና ጉዳዮችን በአብዛኛው ችላ የሚሉ ነበሩ። ስለሆነም፣ ብዙ ሰዎች በደንብ ያልጸዳ እጆችን ተጠቅመው በጋራ ምግብ ውስጥ ያለውን ዳቦ በመስበር እና በትልቁ የመመገቢያ ሰሃን ላይ በመቀላቀል በሽታ ሊያመጡ የሚችሉ ተህዋሳትን በእጃቸው አማካኝነት ወደ ምግባችን ያስተላልፉ ነበር ። በዚህ ምክያት ብዙ ሰዎች በተደጋጋሚ ይታመሙ ነበር። እኔ ራሴ የዚህ ንጽህና ጉድለት ሰለባ ሆኜ በክልሉ ሆስፒታል ለሦስት ወራት ያህል በከባድ የተቅማጥ በሽታ የአልጋ ቁራኛ ሆኜ ነበር።

እንዲህ ያለው ክስተት ፣ ሁሉም ሰው አብሮ እንዲበላ በማስገደድ ለህመም ያሚያበቃ የቅርብ ሃላፊዎቹ ግትር አስተሳሰብ ውጤት ነበረ ሊባል ይቻላል። ጉዳዩን ቢያውቁትም፣ አንድም የባለስልጣን አካላት ሁኔታውን ለማስተካከል እርምጃ የወሰደ አልነበረም። ሃላፊዎቹ የሌላ ሰው ምክር ለመስማት ፈቃደኛም አልነበሩም። ምንም እንኳን በብሔራዊ አገልግሎት ወቅት ያልተፈለገ ምክር መስጠት ወይም እውቀትን ማካፈል ቅጣትና ማሰቃየትን የሚያስከትል ቢሆንም፣ አንዳንዶች ምሁራን ጉዳዩን በማስረዳት የወታደሮቹን የጤና ሁኔታ ለማሻሻል ሞክረዋል። ይህም መረጃ በሌላቸው ወይም ባልተማሩ ግለሰቦች የመመራት ፈተናዎች ከባድ መሆኑን ያሳያል።

ዓሰብ እስርቤት

አንድ ቀን ክፍላችን ከሚመራው ኮሎኔል ጋር ወደ አሰብ ከተማ ተጓዝን። ኮሎኔሉ ወደ አሰብ ወታደር እስር ቤት ያመራ ስለነበረ እኔንም ወደዛው ወሰደኝ። እንደደረስንም እሱ ሊጎበኘው ወደሚፈልገው ቢሮ አመራ ። እኔም ዙሪያውን እየተመለከትኩ በሩ ላይ ቆየሁ።

በዚያ የታዘብኩት ነገር በጣም የሚያስደነግጥ ነበር፣ አንድ ረጅም ጡንቻ ያለው ሰው በብረት ሰንሰለት የታሰረውን ወጣት እየገረፈ ነበር ያየሁት። የወጣቱ እግሮች በካቴና ታስረው ከአንገቱ ጎንበስ ብሎ ነበር። ሙቀቱ ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ነበር። በላብ ተሸፍኖ እና በሲቃ ለቅሶ እህ እህ እህ ይልነበር። ልቤ ስለ እሱ አዘነ፣ እናም እንዲህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት ቅጣት እንዲደርስበት ምን ቢያደርግ ነው ስል ራሴን ጠየቁ። ከዚህ በፊት፣ አንድ ሰው በሌላው ሰው ላይ እንዲህ ዓይነት ጥቃት ሲያደርስ አይቼም ሰምቼም አላውቅም ነበር እናም ሁኔታው በጣም ረበሸኝ። ሁኔታው ነብሴን አስጨነቃት እና በተቻለ ፍጥነት ሃገር ለቆ መሄድን  ተመኘሁ።

በኋላ ኮሎኔሉ መጣና ወደ ሰፈራችን ተመለስን። ጭንቀቴን ለራሴ ልይዘው አልቻልኩም እና ስለአየሁት ቅጣት ኮሎኔሉን ጠየቅኩት። ስለ ወጣቱ የተሰማኝን ስሜት ነገርኩት። ኮሎኔሉ እንዲህ ሲል መለሰ ፣ ” እንዲህ ያለ ከባድ ቅጣት ህግን ለማክበር ላልቻሉ ሰዎች የሚሰጥ ነው አለ” ። ከዛም “አትጨነቅ፤ ህግን እስካከበርክ ድረስ እንደዚህ አይነት ቅጣት አይደርስብህም” ሲል አረጋጋኝ።

በእኔ እምነት ይህ ዓይነቱ ቅጣት ትምህርት የሚያስገኝ አይመስለኝም ፣ እንዲያዉም ድርጊቱ ለመግደል የታሰበ እንጂ ለማስተማር ታስቦ የሚደረግ ቅጣትም አይመስልም ነበር።

ሻዓቢያን መረዳት፣

ጊዜ እየሄደ ሲመጣ፣ በምናቤ የማሰላስለው ሻዓቢያ እና እውነተኛው ሻዓቢያ ፍፁም የተለያዩ መሆናቸውን ተረዳሁ። ፕሮፓጋንዳቸው ለብዙ ኤርትራዊያን የተሳሳተ ምስል ይሰጥ ነበር ቢባል እዉነት ነው። እንደውም በኣስመራ የሚኖሩ ኤርትራውያን እንኳን መንግሥታቸውን በሚገባ ሊረዱት በማይችሉበት ሁኔታ፣ ምንም ኣይነት መረጃ የላቸዉም ወይም ኣያገኙም። መንግስታቸው ከስህተቾች ነጻ እንደሆነ ነው የሚያስቡት። መንግስት ከፍልጠት ነጻ እንደሆነም ገና በደንብ አልተገነዘቡትም። የመንግስት እዉነተኛ ገጽታ የሚታወቀው ወደ ብሔራዊ አገልግሎት ሲኬድና ወታደር ሆነህ ማገልገል ስትጀምር ብቻ ነው። በዚህ ግዜ ነው አረመኔነታቸው እና መሃይምነታቸውን በቀላሉ መገንዘብ የሚቻለው። መሪዎቹ የትምህርት እና የስራ ልምድ የሌላቸው፣ በሥነ ምግባር ያልታነጹ እና ብቃት የሌላቸው መሆናቸዉን መገንዘብ ይቻላል። በስረዓት ታንጾ እና አብሮ የመኖርን ህግ እያከበረ ለኖረ ሰው፣ ከነዚህ ሰዎች ጋር መኖር በጣም ጥንታዊ እና ጨቋኝ በሆነ አካባቢ ውስጥ እንደመኖር ያህል ይሰማዋል። በዚያ መኖር በእንሰሳ የመኖሪያ ስፍራ ዉስጥ ከእስሳት ጋር እንደመኖር ነው የሚቆጠረው።

በአሁኑ መረዳቴ ሻዓቢያ እንደሚታሰበው ሳይሆን፣ የ 30 ዓመት ትግሉ ለሕዝብ ነፃነት ሳይሆን ለግል ጥቅም የታገሉ እንደሆነ በደንብ ተገልጾልኛል። ሁሉንም ነገር ለግልና ለራሳቸው ጥቅም በማዋል፣ የኢትዮጵያን መንግስት ለመገልበጥ ኤርትራዊያንን እንደ ወታደር ተጠቅመው፣ በመጨረሻም የታገለዉን ህብረተሰብ ሆነ ወታደር ክደዋል። በሚያሳዝን ሁኔታ ብዙ ወጣቶችን ከሀገር ለቀው እንዲሰደዱ በማድረግ እና ስለ ድርጊታቸው ጥያቄ ያነሱ እውነተኛ ኤርትራውያንን በዘዴ በማሰቃየት ገድለዋል። በተጨማሪም ዲያስፖራውን በማሳሳት ድጋፍ በማግኘት እስከ ዛሬ ድረስ ንጹሃን ኤርትራውያንን መበዝበዙን ቀጥለዉበታል።

የዲያስፖራው ህብረተሰብ በስሜት የሚነዳ ህብረተሰብ በመሆኑ ወንድሞቻቸው ላይ የሚደረገዉን ግፍ ሳይመረምሩ ፣ በስሜት መንግስትን የሚደግፉ ሆድ አደሮች በመሆናቸው፣ የዚህ ህብረተሰብ እካል መሆን በራሱ አሳፋሪ ነገር ሆኖዋል። መገንጠሉ ቀርቶ ምን ኣለበት እንደድሮው በሰላም ከኢትዮጵያ ጋር ተቻችለን ብንኖርስ ያስብላል። በቀድሞው ስረዓት ይፈጸም የነበርው ግፍም ቢሆን ዋንኛው ምክንያት እራሱ ሻዓቢያ ስለነበር ፣ ሰላምን ለማምጣት ፣ ደርግን ከመዋጋት ይልቅ ሻዓቢያን መዋጋቱ ነበር የሚያዋጣው ቢባል ትክክል ይሆናል ።

ከቅዠቴ ስመለስ፣

እስከ አሁን ያለው የኤርትራ ማህበረሰብ የሲቪል መዋቅር በብቃት ላይ የተመሰረተ አይደለም። ወታደራዊ መዋቅሩም ቢሆን እንደዛው ነው። ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ባለሥልጣናት ከፍተኛ የተማሩ ባለሙያዎችን ያስተዳድራሉ። መሐንዲሶችን እና ዶክተሮችን ለወታደራዊ መሪዎች የግል አገልጋይ እንዲሆኑና በህርሻ ቦታዎች ላይ የግል እርሻ ኮትኳቾችና ሳር አጫጅ የሚያደርጉበት ስረዓት እስከ ምን ድረስ የደከመ እና እርባና የሌለው መንግስት መሆኑን ያሳያል። ጨቋኝ ስርዓት የማይታዘዙትን ሁሉ ይቀጣል። ሁሉንም ሰው በወኪሎቹ አማካኝነት እየተከታተለ፣ የግል አስተሳሰብ ጡዘቶችን ሳይቀር በአሰቃቂ ሁኔታ ይቆጣጠራል። ይህ አሰቃቂ እውነታ በኤርትራ እንደቀጠለ ሆኖ፣ የተቀረው ዓለም ግን ዞር ብሎ ማየቱ ተስኖት፣ እንደፈረስ ወደፊት ብቻ እያየ መሰጎሙን ቀጥሎዋል። እንዲህ ያለ ግፍ በጃንሆይም ዘመነ መንግስት ወይም በደርግ ዘመነ መንስግስት በኤርትራዊያኖች ላይ አልታየም።

የኤርትራ ቆይታዬ የነበረኝን የተሳሳቱ አመለካከቶች ሙሉ በሙሉ እንዳስወግድ አግዞኛል ። የነፃነት ተስፋዎች በፍርሃት፣ በጭቆና እና በማታለል ስልት ተቀብሮዋል። ኤርትራ የነጻነት ህልሟ በጭካኔና በግፍ ተወስዶዋል ።

መደምደሚያ

አሁን በኤርትራ ያለው አገዛዝ ፣ ዜጎች በገዛ ወገኖቻቸው ላይ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያስገድድ ስርዓት ነው። ዜጎቹን ለእስር እና ለጥቃት ይዳርጋቸዋል። ይህ አስጨናቂ ሁኔታም በሀገሪቱ ውስጥ ድብቅ አጀንዳዎች እንዳሉ ያሳያል። በተለይ ግለሰቦች በቤተሰባቸው አባላት ላይ በደልና ግፍ ሲፈጽሙ ማየት የህብረተሰቡን የዘቀጠ የሥነ ኣእምሮ ቀዉስ የት እንደደረሰ ያሳያል። እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ከሥነ ምግባር አኳያ ችግር ያለበት ነው። ለግል ጥቅማቸው ሲሉ እንዲህ ያለውን ጭካኔ ከሚያራምዱ ማህበረሰብ ጋር ደሞ ኣብሮ መደመር አሳፋሪ ነው።

ህይወትን ከነዚህ ሁኔታዎች አንፃር ስንመለከታት ፣ የራሱን ዜጎች ከሚበድል ሥርዓት ጋር አብሮ ከመኖር አገር አልባ ሆኖ መኖር ይመረጣል።

ዲቮራ (የብእር ስም)

LET’S KEEP IN TOUCH!

አዳዲስ ጽሁፎች እንዲደርስዎ ይመዝገቡ

This field is required.

የንግድ ማስታወቂያዎችን አንልክም ።